[gtranslate]

አሜሪካና የተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮች ከኢትዮጵያ ምንድን ነው

የሚፈልጉት? ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ሲሳይ አጌና በኢሳት ቴሌቪዥን ላይ ጋብዞት

ላቀረበለት ጥያቄ  ለሰጠው ሀተታ ትችት!

 

          ፈቃዱ በቀለ( ዶ/ር)

ሚያዚያ 01፣ 2021

መግቢያ

ከአራት ቀናት በፊት ሲሳይ አጌና ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉን፣ በኖርዝ ካሮላይና ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ አስተማሪና ዲፕሎማት ሆኖ የሰራውን አሜሪካና የተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮች ለምን በአሁኑ በዶ/ር አቢይ በሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ላይ የዲፕሎማቲክ ግፊትና እስከማስፈራራትም የሚደርስ ጫና እንደሚያደርጉ ብዙ ጥያቄዎችን አንስቶለት በሚመስለውና በሚረዳው መልክ የራሱን አስተያየት ለመስጠት ሞክሯል። የሱን የቃለ-መጠይቅ ምልልስ ካዳመጥኩኝ በኋላ የቀረቡለትን ትችቶች በዝርዝር ስመለከት ወደ 99% በላይ የሚሆኑት የቃለ-መጠይቁን ምልልስ ያዳመጡት በጣም ጥሩና ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ለመገንዘብ ችያለሁ። በተለይም ፕሮፌሰሩ አሁን አገራችንን በሚቆጣጠረው በዶ/ር አቢይ አገዛዝ ላይ ያለው ዕምነትና ትችታዊ ባልሆነ መልክ ያቀረበው ሀተታው አብዛኛዎችን አስድስቷቸዋል።

ወያኔ ስልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊትም ሆእ በኋላ የአሜሪካንና የተቀሩትን የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት አገሮች የውጭ ፖለቲካ አስመልክቶ በሰፊው በቲዎሪ፣  በታሪክና በማስረጃ በተደገፈ መልክ በመጻፍ ለአንባብያን አቅርቤያለሁ። አንባቢው በየጊዜው ያቀረብኳቸውን ሰፋፊ ሀተታዎችን አንብቦ በቂ ግንዛቤ ማግኘት ችሎ እንደሆን ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ካቀረብኳቸው ሰፋፊ ጽሁፎች ውስጥ፣ በተለይም ለሻለቃ ዳዊት የሰጠሁት መልስ፣ „ጦርነቱ የአፍሪካውያን አይደለም፣ የአሜሪካና የአውሮፓውያን ነው“፣ የሚለውና፣ „ከአምባገነን ባሻገር፣ የተወሳሰቡ ነገሮችን መረዳት“ በሚል በተለይም ስለ ኢምፔሪያሊዝም ምንነት የሚያወሳውን ሰፊ ሀተታ፣ „የኢትዮጵያ ጠላቶች ማናቸው“ የሚልና፣ በተጨማሪም „ስለዘራፊ መንግስትና አነሳሱ…ወዘተ. „የሚሉ ሰፋፊ ጽሁፎችን በማቅረብ አንድን አገር በማዳከምና የመጨረሻ መጨረሻም ማፈራረስ የውስጥ ኃይሎችና የውጭ ኃይሎች ያላቸውን የተሳሰረ ግኑኝነት ለማሳየት ሞክሬያለሁ። ከሁለት ወር በፊት ደግሞ „ጥቁሩና ነጩ ጁንታ“ በሚል እንደዚሁ ሰፊ ሀተታ በማቅረብ በወያኔና በአሜሪካን መሀከል ያለውን የጥቅም ግኑኝነትና አገርንና ባህልን የማፈራረስ ተልዕኮ ለማሳየት ሞክሬያለሁ። ከዚህም በተጨማሪ ስለአገር ወዳድነት ስሜት የሚያትት ሁለት ተከታታይ ጽሁፎችን በማቅረብ አንባብያኑ፣ በተለይም ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያለ ለሚጮኸው በቂና ጥልቀት ያለው ግንዛቤ እንዲያገኝ ለማድረግ ሞክሬያለሁ።

ይህ ሁሉ ሀተታ ከተጻፈ በኋላ ይህንን ሁሉ የሚከልስና በተለይም ወጣቱ በቂና ትችታዊ ግንዛቤ እንዳያገኝ ከፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ለሲሳይ አጌና  የአሜሪካንና የተቀረውን የካፒታሊስት አገሮች  በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን አመለካከትና አሁን ደግሞ ስለሚያደርጉት ግፊት የሰጠውን ሀተታ ሳዳምጥ ዝም ተብሎ መታለፍ እንደማይችል ለመረዳት በመቻሌ ይህንን ትችት ለመጻፍ ተገድጃለሁ። ፕሮፌሰሩ የሰጠውን ገለጻ ሳዳምጥ በዕውነተኛ የፖለቲካ ሳይንስ መነጽር ብቻ ሳይሆን በቲዎሪና በኢምፔሪካል ደረጃ የሚደገፍ አይደለም። ፕሮፌሰሩ በተቀላጠፈ መልክና ፈጠን ፈጠን እያለ ስለሚናገር፣ በተለይም በቂ ዕውቀት የሌላቸውንና ጠጋ ብለው የዓለምን ፖለቲካ ለማይከታተሉ የሰጠው አስተያየት አብዛኛውን አዳማጭ የማሳሳት ኃይሉ በጣም ከፍ ያለ ነው። አብዛኛዎችንም ለማሳመን ሞክሯል።

በአጠቃላይ ሲታይ ፕሮፌሰር ብሩክም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ምሁራኖችና፣ የአገራችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ በየጊዜው ለተለያዩ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች የሚሰጧቸው ሀተታዎች አብዛኛዎቹ በሳይንስ የማይደገፉና የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታና የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ላይ የሚጫወተውን አሉታዊ ሚና የማያንፀባርቁና ለአዳማጩም ሆነ ለአንባቢው በቂ ግንዛቤ የማይሰጡ በጣም አሳሳችና ትጥቅ አስፈቺ ሆነው አግኝቼአቸዋለሁ። ሀተታዎቻቸውንም ሆነ ገለጻዎቻቸውን ሁሉ በደንብ ለተመለከተ የተለያዩ ምሁራን የሚሰጡት ገለጻ አገራችንን ለሚቀጥሉት ሺህ ዐመታት ደሀና ደካማ ሆና እንድትቀር የሚያደርጋት መሆኑ ግልጽ ነው። ሀታተቸውንም በደንብ ላነበበና ለሚያነብ ጸሀፊዎችም ሆነ ለቃለ-ምልልስ መልስ የሚሰጡት የኢትዮጵያ ህዝብ ከድህነት መላቀቅ እንዳለበትና፣ ኢትዮጵያም እንደ አገርና እንደ ማህበረሰብ በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት እንዳለባት እንደማያሳስባቸውና ጭንቅላታቸውም ውስጥ እንደሌለ ነው።  በአጠቃላይ ሲታይ እኛ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተንታኞች ከሌሎች የአፍሪካ ምሁራን ጋር ስንወዳደር እጅግ ወደ ኋላ የቀረንና፣ በተለይም ደግሞ ለአሜሪካንና ለተቀረው የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮች ተንበርክከን እንድንገዛ የሚያደርገንና የእነሱን የበላይነት አሜን ብለን እንደተቀበልን ነው ሁኔታው የሚያረጋግጠው።

አንድ ነጻና ጠንካራ ማህበረሰብ ለመገንባት ከፈለግን የግዴታ ብዙ ነገሮችን ግልጽ ማድረግ ያለብን ይመስለኛል። አገር፣ ሀብረተሰብ፣ ሰው፣ ባህል፣ ፖለቲና ኢኮኖሚ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ…ወዘተ በመሳሰሉት ነገሮች ላይ ግልጽነት እስከሌለን ድረስና፣ በተለይም ደግሞ አንዳንድ ፕሮፌሰሮች በሚሰጡት ገለጻ በቀላሉ የምንታለል ከሆነ ኢትዮጵያ የምትለውን አገር መርሳት ያለብን ይመስለኛል። እንደ እኔ የመሰለውም እንደዚህ ዐይነት አሳሳች ገለጻዎችና አጻጻፎች በሚቀርቡበት ጊዜ ጊዜዬንና ገንዘቤን እያፈሰስኩ የምደክምበት ምክንያት አይታየኝም። ሁኔታውም በዚህ ሊቀጥል አይችልም። ስለሆነም ከሁለት አንዱን በግልጽ መለየትና መቀበል ያለብን ይመስለኛል። አይ ለጠንካራና ለነጻ ኢትዮጵያ መታገል፣ አሊያም ደግሞ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት አገሮች ለምትታሽና ደካማና ለፈስፋሳ ሆና ለምትቀር አገር መታገል። ከሁለቱ አንዱን መምረጥ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በተረፈ ትችታዊ አመለካከት ያላቸውና ለአገራቸው ተቆርቋሪ የሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ምሁራን የበኩላቸውን አስተዋጽዖ የማያደርጉና የማያግዙ እስከሆነ ድረስ አንድ ሰው ብቻውን የሚደክምበትና ኃይሉን የሚጨርስበት ምክንያት የለም። ከሁሉም ሰው ጋር በሃሳብ መጋጨት ወይም ደግሞ የተሳሳተ አስተሳሰብ በሚቀርብበት ጊዜ ለሱ መልስ መስጠት ሊያስገምትና ጠላትም ማፍራት ይቻላል። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ አድፍጦ የሚጠባበቅ ኃይልንም ማሳመን አይቻልም። ለማንኛውም ወደ ዋናው ቁም ነገር ልግባ።

በእርግጥስ አሜሪካና የተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም የኢትዮጵያን ጥንካሬ ይፈልጋል ወ?  

ሲሳይ አጌና ለምን አሜሪካንና የቀሩት የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮች በዶ/ር አቢይና በአገራችን ላይ ግፊት ያደርጋሉ? ብሎ ላቀረበለት ጥያቄ ፕሮፈሰር ብሩክ በቀጥታ ለጥያቄው መልስ ከመስጠቱ በፊት እንደሚከተለው አጠቃላይ ገለጻ ስጥቷል። ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ነች፣ የህዝብ ቁጥሯም ከፍ ያለና እየጨመረ የሚመጣ ነው፤ ስለዚህም ይህንን ሁሉ ህዝብ መመገብ ያስፈልጋል፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ማዕከለኛውን ቦታ የያዘች ነች፤ ስለሆነም ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ከሌለ በአካባቢው ያሉ አገሮች ብቻ ሳይሆኑ፣ ጠቅላላውም አፍሪካ የመናጋት አደጋ ያጋጥመዋል። ይህ ከሆነ ደግሞ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ አገሩን ጥሎ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ይጎርፋል፤ ስለዚህም ይህ እንዳይሆን ይፈልጋሉ፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ሰላምን በማስከበር ከፍተኛ ሚና የተጫወተችና በዚህም የምትታወቅ ነች፤ ኢትዮጵያ በተለይም ሸበርተኝነትን በመዋጋት ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች፤ አልቃይዳ፣ አልሻባብና ከቅርብ ዐመታት ጀምሮ በማሊና በኒጀር በእስላም አክራሪዎች የሚካሄደው ሽብርተኝነት…ወዘተ. ይህ ሁሉ ነገር በቀጥታ አሜሪካንና የተቀረውን የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮች የሚመለከት ስለሆነ የኢትዮጵያን መዳከምና መፈራረስ አይፍልጉም ይለናል። በተጨማሪም ለምንድን ነው በተለይም የወያኔ አገዛዝ ከተዳከመ በኋላና እንደገና ስልጣን ላይ ለመመለስ ያለው ዕድል በጣም የመነመነ ከሆነ በአዲሱ የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ላይ እንደዚህ ዐይነት ጫና የሚያደርጉት? ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄም እንደዚህ በማለት መልሷል። እንደሚታወቀው አሜሪካኖችም ሆነ የተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ለብዙ ዐመታት ከህውሃት ጋር አብረው ሰርተዋል፤ በደንብ የሚያውቁትም የህውሃትን አገዛዝ ነው። መንግስታቱም ከስለላ ድርጅቶቻቸውና ከሌሎች አካሎቻቸው የሚሳጠቸው ሀተታ ለየት ያለና፣ እነሱም ስለ አገራችን ያላቸው ግምት ለየት ያለ ስለሆነ ሁኔታውን የሚጠባበቁና፣ በሚሰጣቸው መረጃ መሰረት ህውሃት ተመልሶ ስልጣን ላይ የመምጣት ኃይሉ ከፍ ያለ ነው የሚል ግምት ነበራቸው። ከዚህም በላይ የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ያልተደላደለና ወዴትም እንደሚያመራ ስለማይታወቅ የግዴታ ህውሃት ተመልሶ ስልጣን ላይ ሊወጣ ይችላል የሚል ዕምነት ነበራቸው ይለናል። ከማያውቁት መልአክ፣ በደንብ የሚያውቁት ዲያብሎስ ይሻላል እንደሚሉት ዐይነት ነው ፖለቲካቸው ማለቱ ነው።

ይሁንና ይላል፣ እንደዚህ ሲባል ግን አሜሪካኖችም ሆነ የተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ኢትዮጵያን የሚፈልጓት ከጥቅማቸው አንፃር  ብቻ በማየት ነው ይለናል። በተለይም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም፣ የጂኦ ፖለቲካ ጠቀሜታና ሌላም ሌላም ጥቅሞች አላቸው ይለናል። በሌላ ወግን ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር የለም። የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ ለማካሄድ፣ ይህስ ከሆነ ምን ዐይነት የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ፣ የፍጆታ ዕቃዎችን ለማራገፊያ ብቻ፣ ወይስ ጥሬ-ሀብትን ለማውጣትና ፍራፍሬዎች በማስተከል ወደ አሜሪካ መውሰድ…ወዘተ. በማለት አብራርቶ የገለጸው ነገር የለም። በአንፃሩ ደግሞ ኢትዮጵያ አሜሪካንንም ሆነ አውሮፓን የምትፈልገው በቀጥታ ከእነሱ ዕርዳታ ለማግኘት ነው ይለናል። ይሁንና ግን በዕርዳታ አማካይነት ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ስርዓት ሊገነባ እንደሚችልና፣ ኢትዮጵያም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን ትበቃ አትበቃ እንደሆን ያስረዳው ነገር የለም።  ይህንን በሚመለከት ከጋዜጠኛው ከሲሳይ አጌና ለፕሮፌሰሩ ክሪቲካል ጥያቄ አልቀረበለትም። አንደኛ፣ ዕርዳታ ሲባል ምን ማለት እንደሆነና፣ በተለይም በወያኔ ዘመን በዕርዳታ ስም የፈሰሰው በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብና ሌሎች ቁሳቁስ ነገሮችም አገራችንን ለምንስ ራሷን እንድትችል ለማድረግ አላስቻሏትም? እስከመቼስ ድረስ ነው ዕርዳታ የሚያስፈልጋት? ብሎ ለመጠየቅ አልቃጣም። ከዚህም በተጨማሪ  ወያኔ 27 ዓመታት ያህል የኢትዮጵያን ህዝብ እንደዚያ ረግጦ ሲገዛና ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት መጣስ ሲታይ ለምን የምዕራቡ ዓለም ዝም ብሎ ተመለከተ? የሚለውን አስፈላጊ ጥያቄ በፍጹም አላነሳም። ከዚህም በላይ ዲሞክራሲን፣ ብዝሃዊነትን፣ የህግ የበላይነትን፣ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚንና፣ በአጠቃላይ ሲታይ የሊበራል ዲሞክራሲን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት እፈልጋለሁ የሚለው አሜሪካንም ሆነ የተቀረው የካፒታሊስቱ ዓለም ለምን በአገራችን ምድር የምዕራቡን እሴቶች በሙሉ የሚጻረር የጎሳ ፌዴራሊዝምንና ከዚህ ጋር ተያይዞ አገሪቱን ለብዙ ዓመታት እንዳትረጋጋ የሚያደርጋትን ፖሊሲ ህውሃት ሲከትል ዝም ብሎ ተመለከተ? ብሎ አልጠየቀውም። ከዚህም በላይ መነሳት የነበረበት ጥያቄ በወያኔ አገዛዝና በአሜሪካኖች መሀከል የነበረው ግኑኝነት ምን ዐይነት ግኑኝነት ነበር? በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ወይስ የጌታና የሎሌ ዐይነት ግኑኝነት? ብሎ ለመጠየቅ አልቻለም፤ ሃሳቡም የመጣለት አይመስለኝም።

ከጥያቄዎችም ሆነ ከተሰጡት መልሶች ስነሳ ጠያቂውም ሆነ ተጠያቂው ስለዓለም ፖለቲካ፣ በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማለቂያ በኋላ ስለተዋቀረው የኢኮኖሚና የሚሊታሪ ሁኔታና፣ ስለአሜሪካን የውጭ ፖለቲካና፣ በተለይም ደግሞ የኮሙኒስቱ ዓለም ከፈራረሰ ከ1989 ዓ.ም በኋላ ስለተፈጠረው አዲስ ሁኔታና፣ የኮሙኒስቱ ዓለምስ ከፈራረስ በኋላ ከሰላምና ከብልጽግና ይልቅ ጦርነትና ድህነት ለምን በዓለም አቀፍ ደረጃ  እንደተስፋፉ ግልጽ የሆነላቸው አይመስለኝም።

ለማንኛውም በአጠቃላይ ሲታይ በተለይም በአሜሪካና በኢትዮጵያ መሀከል ስላለውና ስለሚኖረው ግኑኝነት በመሀከላችን ያለው ዕምነት አሜሪካን ኢትዮጵያን አጥብቆ እንደሚያፈቅራትና፣ እንደ አንድ ብቸኛ ልጁም ምንም ነገር እንዳይደርስባት ተንከባክቦ እንደሚይዛትና፣ ኢትዮጵያና አሜሪካም እንደሚፈላለጉ ነው። ይህ ዐይነቱ አመለካከት በተለይም ባለፉት 70 ዓመታት በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የተዋቀረውን ዓለምና የሚከተለውን አግሬሲቭ ፖለቲካ የሚቃወምና፣ አሜሪካም በተለየ መልክ ኢትዮጵያን እንደማያፈቅራት ነው። አሜሪካን እንዴት እንደ አገር እንደተመሰረተና፣ የኃያልነት ሚናን ለመጎናጸፍ እንደቻለ ግልጽ የሆነ አመለካከት ቢኖር ኖሮ  ሀተታውና በአሜሪካንና በኢትዮጵያ መሀከል ስለነበረውና ስላለው ግኑኝነት ለየት ባለ መልክ ሊቀርብ በቻለ ነበር።

እንደሚታወቀው በአሜሪካንና በኢትዮጵያ መሀከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግኑኝነት ለመረመረ በአፄው ዘመንም ሆነ የኋላ ኋላ ደግሞ በሶሻሊዝም ስም የሚታማው የደርግ አገዛዝ ከወደቀና ህውሃት በአሜሪካንና በእንግሊዝ መንግስት ድጋፍ ስልጣንን ከተቀዳጀ ወዲህ በዚህ ዐይነቱ የጌታና የሎሌ ግኑኝነት መሰረት የኢትዮጵያ ህዝብ ተጠቃሚ ሊሆን አልቻለም። ህዝባችንና አገራችንም በጠንካራ መሰረት ላይ ሊቆሙ አልቻሉም። ሳይንስና ቴክኖሎጂም የኢኮኖሚው መሰረት በመሆን ህዝባችን አለተሳሰረም። በአንፃሩ የኢትዮጵያ መንግስታት ከአሜሪካን  ጋር ልዩ ዐይነት ግኑኝነት በመመስረታቸው ከረጅም ጊዜ አንፃር ሲታይ ወደ ውስጥ የተረጋጋ ሁኔታ እንዳይፈጠር ለማድረግ ተችሏል። ይህንን ትተን የካፒታሊዝምን ሆነ የኢምፔሪያሊዝምን ውስጣዊ ባህርይና ዕድገቱን ስንመለከት ከውስጥም ሆነ ከውጭ እኩልነትን አይፈልግም። በአፈጣጠሩ ካፒታሊዝም ህዝብን እያፈናቀለና በመበዝበዝና ትርፍን በማካበት ነው የተመሰረተው። ከውጭው ዓለም ጋር የነበረውንና የአለውን ግኑኝነት ስንመረምር ደግሞ የአሜሪካንም ሆነ የተቀረው የካፒታሊስት ዓለም ሶስተኛ ዓለም ተብለው የሚጠሩ አገሮችን፣ በተለይም አፍሪካን በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሚሊታሪያዊና የስለላ መሳሪያዎች በመጠቀም ነው ራሳቸውን ለማደለብና በተለይም ደግሞ አፍሪካን ለማቆርቆዝ የቻሉት።  በተለይም የአሜሪካን ካፒታሊዝም ከአውሮፓው ጋር ሲወዳደር የረጅም ጊዜ የባህል ክንዋኔ ያልተካሄደበት በመሆኑ አስተዳደጉ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በመግደልና ጥቁሩን ደግሞ በፕላንቴሽን ኢኮኖሚ ውስጥ በባርነት በማሰራት ነው ሊያድግና ሊያብጥ የቻለው። ስለሆነም ወደ ውጭም የሚከተለው ፖለቲካ ይህንን የሚያንፀባርቅ እንጂ ሌሎች አገሮች ዕድገትንና የተሟላ ዲሞክራሲን እንዲጎናጸፉ የሚያደርግ አይደለም። በአፍሪካም ሆነ በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች በነፃ ገበያና በሊበራሊዝም ሽፋን ስም የተካሄዱትና የሚካሄዱት የጥገና ለውጦች በሙሉ ወደ ውስጥ ዕውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን የፈጠሩና፣ የተሟላና የተሳሰረ የኢኮኖሚ ዕድገትን ያመጡ ሳይሆኑ በየአገሮች ውስጥ አምባገነናዊ ስርዓቶች እንዲፈጠሩና እንዲፈረጥሙ ያመቻቹ ናቸው። ለዚህም ነው ወያኔ ስልጣን ከጨበጠ በኋላ ተግባራዊ ያደረገው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲና የጎረፈለት የስለላ መሳሪያ አምባገነናዊና አረመኔያዊ ሊያደርገው የቻለው።

በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የእንግሊዝን ሚና ከወሰደ ከ1945 ዓ.ም ጀምሮ በአዋቀረው ልዩ ዐይነት የሚሊታሪና የስለላ መሳሪያና፣ ባረቀቀውም አሳሳች የትምህርት ፖሊሲ አማካይነት ብዙ አገሮችን በራሱ ቁጥጥር ስር ለማድረግ ችሏል። ከቁጥጥሩ ለመውጣት የፈለጉትን ከኢራን ጀምሮ እስከ ቺሌ ድረስ በአገዛዝ ግልበጣ በመሳተፍ በሁለቱም አገሮች አሰቃቂ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ለማድረግ በቅቷል። በጊዜው የሞሳዴክም ሆነ የፕሬዚደንት አሌንዴን መንግስት ለተመለከተ፣ ሁለቱም ከበርቴያዊ መንግስት ለመመስረት፣ ለዚህ ደግሞ በኢንዱስትሪ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚ እንደሚያስፈልጋቸው በመረዳታቸው አሜሪካንን የሚጎዳ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ይጀምራሉ። በእንግሊዝና በአሜሪካን ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር የነበሩ ኢንዱስትሪዎችንና የዘይት ማጣሪያዎችን በመንግስት ቁጥጥር ስር በማድረጋቸው ሁለቱም እንዲቀጡ ይደረጋሉ።

ከዚህና ከአያሌ ኢምፔሪካል ጥናቶች ስንነሳና፣ አሜሪካንም ከኢትዮጵያ ጋር የነበራትን ግኑኝነት በምንመረምርበት ጊዜ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምም ሆነ የተቀረው የካፒታሊስቱ ዓለም የኢትዮጵያን ጥንካሬ የሚፈልጉ አይደሉም። ደካማና ከቁጥጥራቸው ስር መውጣት የማትችልን ኢትዮጵያን ነው የሚፈልጉት። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ በልዩ ልዩ ተቋማት የተደገፈ ኢኮኖሚ፣ በተለያየ የመገናኛና የመመላለሻ ግኑኝነቶች የተሳሰረ አገር የአሜሪካንንም ሆነ የተቀረውን የምዕራብ አውሮፓ ጥቅም የሚያናጋና ተፎካካሪም ስለሚሆን ነው። ነገሩን በይበልጥ ለመረዳት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ከተተከሉ ያሉንን የእርሻና የጥሬ ሀብቶች ከመጀመሪያው ጀምሮ በፋብሪካ ውስጥ እንዲከናወኑና እዚያ አገራችን ምድር ለገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ ሰፊው ህዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ እንችላለን። በዚህም መሰረት ሰፋ ያለ የስራ መስክ ሲከፈት፣ በገንዘብና በምርት መሀከል የሚኖረው ግኑኝነት ይጠነክራል። ይህ ብቻ ሳይሆን አገራችንና ህዝባችን በተለያዩ የፍጆታ ዕቃዎች ራሳቸውን የሚችሉ ከሆነ ከውጭ የሚመጣው የፍጆታ ዕቃ መጠንም ይቀንሳል። በዚያው መጠንም ጤናማ የሆነ የንግድ ሚዛን ይፈጠራል፤ ከአጭር ጊዜ አንፃር የዕዳ መጠናችን ሲቀንስ፣ ከረጅም ጊዜ አንፃር ደግሞ ከዕዳ የምንላቀቅበት ሁኔታ ይፈጠራል፤ ህዝባችንም እንደነፃ ዜጋ የመኖር ዕድሉ ከፍ ያለ ይሆናል። ይህንን ዐይነቱን ሁኔታ አሜሪካንም ሆነ የተቀረው የምዕራቡ የካፒታሊስት አገር አይፈልግም። በተቻለ መጠን እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገሮች እዚያው በዚያው እየተንደፋደፉ የሚቆዩበትን ሁኔታ ነው የሚያመቸችውና የሚፈጥረው። ከዚህ አጠር መጠን ያለ ሀተታ ስንነሳ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ለማብራራት ያልቻለው አያሌ ነገሮች አሉ። ከአጠቃላዩ የኢምፔሪያሊዝምም ባህርይ ስንነሳ አሜሪካንም ሆነ የተቀረው የምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም የሌሎችን አገሮች መጠንከር አለመፈለግ ብቻ ሳይሆን፣ ባህላቸውንም ያወድማሉ። ባህልና እሴት የሌለው አገር ደግሞ እንደ አገርና እንደማህበረሰብ ሊኖር በፍጹም አይችልም። ከዚህ በመነሳት በተለይም በአሜሪካንና በተቀሩት የካፒታሊስት አገሮችና በኢትዮጵያ መሀከል በወያኔ ዘመን የነበረውን ግኑኝነት ጠጋ ብለን እንመልከት።

በህውሃትና በካፒታሊስቱ ዓለም መሀከል የነበረው ግኑኝነት!

ህውሃት እንዴት ስልጣን ላይ ለመውጣት እንደቻለ አብዛዎቻችን በቂ መረጃ እንዳለን እገምታለሁ። ይሁንና ግን አብዛኛውን ጊዜ በእኛ በኢትዮጵያውያን መሀከል አንድን ነገር ከተለያየ አቅጣጫና ክሪቲካል በሆነ መልክ የመመልከት ችግር አለ። የነገሮችን አመጣጥና ዕድገት ለመመልከት ካልተቻለ ደግሞ ፖለቲካ የሚባለውን ግዙፍ ጽንሰ-ሃሳብ የመረዳት ችግር ይኖራል። በፖለቲካ ዓለምም ለመሳተፍና ነፃና ዲሞክራሲያዊ አገርም ለመገንባት በጣም አስቸጋሪ ይሆናል።

ለማንኛውም ህውሃት በአነሳሱ የአሜሪካን ፕሮጀክት ለመሆኑ ግልጽ መሆን አለበት። የአሜሪካንና የእንግሊዝ ፕሮጀክት ለመሆኑ የሚረጋገጠው ደግሞ ተግባራዊ ባደረገው የጎሳ ፌዴራሊዝምና በተከተለው የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ነው። ለምን? ብለው አብዛኛዎች አንባቢዎች ይጠቁ ይሆናል። መልሱ ቀላል ነው። እንደሚታወቀው አንድ አገር በቋንቋና በጎሳ ከተከፋፈለች ከረጅም ጊዜ አንፃር የአንድነት መንፈስ እየተዳከመ ይመጣል። የአንድነት መንፈስ ከተዳከመ ደግሞ የጋራ የሆነ እሴት ሊኖር አይችልም። ቀስ በቀስም የማንነት ጥያቄ የሚሉት ነገር ይነሳል። በዚያው መሰረትም የዋር-ሎርድ አስተሳሰብ በመዳበር ለቁጥጥር የሚያስቸግር የፖለቲካ ሁኔታ ይፈጠራል። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ደግሞ ዞሮ ዞሮ የማዕከለኛው ዘመን ዐይነት የመሳፍንት አገዛዝ አስተዳደር እንዲመሰረት ያግዛል። በዚህ መልክ አንድ አገር ከውስጥ ስትከፋፈልና ስትዳከም ለውጭ ኃይሎችም የምታመች ትሆናለች፤ በቀላሉም ትጠቃለች። በተጨባጭ ሲታይ ሊበራል ዲሞክራሲንና የነፃ ገበያን በዓለም አቀፍ ደረጃ አራምደዋለሁ የሚለው በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚመራው የካፒታሊስቱ ዓለም ለሚያፈቅራትና ለሚወዳት ኢትዮጵያችን ከረጅም ጊዜ አንፃር ልትፈረካከስ የምትችልበትን ሁኔታ ነው ያዘጋጀላት። ይህ ዐይነቱ የጎሳ ፌዴራሊዝም በወያኔ ብቻ የወጣና ተግባራዊ የሆነ ነው የሚል ካለ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦችን በተለያየ መሳሪያ እንዲበላሉ የሚያደርገውን ተንኮል የተረዳ አይደለም ማለት ነው። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ መጻህፍቶች የተተነተነ በመሆኑ የፈቃዱ በቀለ የኮንስፒራሲ ቲዎሪ ነው ተብሎ አይወሰድብኝ። ነገሩን ለመረዳት ስለ አገሬ ያገባኛል የሚል ሰውም ሆነ ድርጅት ጊዜ በመውሰድና ባለመሰላቸት መጽሀፎችን በመፈላለግ ቢያነብ ከጥርጣሬ ሊቆጠብ ይችላል።

ለማንኛውም ይህ ዐይነቱ አንድን አገር ከውስጥ ማዳከም የተለያዩ ገጽታዎች ያሉትና በተለያዩ መሳሪያዎች የሚካሄድ ነው። ከሚሊተሪ አወቃቀርና ጥገኛ ማድረግ አንስቶ ሰላዮችን ማሰልጠንና በስለላ ተቋማት ስር ውስጥ መግባትና መንግስታዊ መዋቅርን ማዳከምና በሰራተኞች መሀከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር ማድረግ፣ በአንድ አገር ውስጥ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል በተለያዩ ጥቅሞች በመግዛትና የራስ ተቀጥያ በማድረግ፣ ተቀጣይ የሆነው ኃይል አገሩን እንዲሸጥና ከውስጥ እንዲዳከም ማድረግ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ያልተስተካከለ ሁኔታ በመፍጠር ህብረተሰቡ ርስ በርሱ እንዲበላላ ማድረግ…ወዘተ. …ወዘተ. እነዚሁ ሁሉ የተለያዩ እንደ እኛ የመሳሰሉ አገሮችን የማዳከሚያ ዘዴዎች ናቸው። ይህንን አገሮችን የማዳከምና ተቀጥያ የማድረግ ተንኮል ለመረዳት የ20ና የ30 ዓመታት የማያቋርጥ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው በአገሮች መሀከል ያለውን ግኑኝነትና፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነት እንዴት ሊስፋፋ እንደቻለ መረዳት የሚቻለው። ካለበለዚያ መዳረቅና ጊዜ ማባከን ብቻ ይሆናል። የሚያሳዝነው ነገር ነፃነትንና ዕድገትን የሚፈልግ የጥንት ታሪክ ያለው ህዝብ በተልካሻና የፖለቲካ ውስብስብነት ባልገባቸው ሰዎች ከአንድ ችግር ወደ ሌላ በመግባት ኑሮው ሁሉ ጨለማ ሲሆንበት ስንመለከት ነው።

ወደ ሁለተኛው የግኑኝነትና አገራችንን ወደ አዳከመው ፕሮጀክት ደግሞ እንምጣ። ህውሃት ስልጣን ላይ ከወጣ ከአንድ ዓመት በኋላ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጠቅላላውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሁለት እግሩ እንዲቆም የሚያደርግ ሳይሆን በነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ስም ወያኔን የሚያደልብ፣ አብዛኛውን ህዝብ ደግሞ የሚያገልና ደሃ የሚያደርገውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ኒዎ-ሊበራሊዝም በመባል ይታወቃል። አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርም ሆነ ፍልስፍናን የተማረ ይህንን ዐይነቱን ፖሊሲ ብቻ ሳይሆን በካፒታሊዝም ግንባታ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ተግባራዊ የሆኑትን የተለያዩ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችንና ፖሊሲዎችን ማወቅ አለበት።

ያም ሆነ ይህ ፖሊሲውን ጠጋ ብሎ ለተመለከተ በካፒታሊዝም ግንባታ ውስጥ እንደዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ሆኖ በፍጹም አያውቅም። ዛሬም ቢሆን አብዛኛዎች የካፒታሊስት አገሮች ንጹህ በንጹህ የኒዎ-ሊበራሊዝምን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ሊያደርጉ አይችሉም፤ ሁኔታውም አይፈቅድላቸውም። እንደሚታወቀው በአብዛኛዎች የካፒታሊስት አገሮች ከ90% በላይ የሚሆነው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በአውቶኖመስ ደረጃ የሚካሄድ በመሆኑ መንግስት በኢኮኖሚ መስክ ውስጥ ገብቶ እንደልቡ የመፈትፈት መብት የለውም። እንዲያውም የመንግስትን የመኖርና ያለመኖር እድል የሚወስኑት ትላልቅ ኩባንያዎች ናቸው። ይህም ማለት መንግስት ጥገኛና ተጎታች ነው ማለት ነው። ጥናቶችና መጽሀፎችም በሙሉ ይህንን ነው የሚያረጋግጡት። በተለይም በቶማስ ፒኬቲ የተጻፉትን ካፒታሊዝም በ21ኛው ክፍለ-ዘመንና ካፒታሊዝምና ርዕዮተ-ዓለም የሚሉትን መጽሀፎቹን ላነበበ በቂ ግንዛቤ ሊያገኝ ይችላል።

ወደ እኛ አገር ስንመጣ ግን መንግስት በሚከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሰረት፣ እንደንቃተ-ህሊናውና እንደ አገራዊ ባህርዩ  ሁኔታ አብዛኛውን ህዝብ የሚጠቅም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ያደርጋል፣ አሊያም ደግሞ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቅም ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ በቴክኖሎጂና በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ ያደርጋል። ሳይንስና ቴክኖሎጂ በማይስፋፉበት አገር ውስጥ ደግሞ እነ ፍሪድሪሽ ሊስትና ሌኒን የውስጥ ገበያ(Home Market)ብለው የሚጠሩት በባቡር ሃዲድ የሚገናኝና በጠቅላላው በአገሪቱ ውስጥ በእሌክትሪሲቲ ሊንቀሳቀስ የሚችል ኢኮኖሚ ሊገነባ አይችልም ማለት ነው። ይህም ማለት ካፒታሊዝም ወይም ደግሞ በዘመኑ አጠራር ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ሊያድግ አይችልም ማለት ነው።

ከዚህ ስንነሳ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ ይታዘዝ የነበረው የህውሃት አገዛዝ የኢኮኖሚንና የህብረተሰብን ህግ የሚጥስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው። ስለሆነም ነው አገራችን ቀስ በቀስ የዕዳ ወጥመድ ውስጥ መግባት የቻለችውና፣ የንግድ ሚዛኗም በከፍተኛ ደረጃ ሊናጋ የበቃው። በዚህም መሰረት ወደ ውስጥ የማምረት ኃይሏ በመዳከሙ የተነሳ ቢያንስ እንደዘይት የመሳሰሉ አስፈላጊ ነገሮችን ማምረት አልተቻለም። በየዐመቱ 400 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በማውጣት ስንዴ ከውጭ እንዲመጣ ይደረጋል። አጠቃላዩን የአገራችንንም የኢኮኖሚም ሆነ የባህል ሁኔታ ስንመለከት በተለይም ወያኔ በአሜሪካኖች ታዞ ተግባራዊ ያደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከፍተኛ የሆነ የሞራል ውድቀትን ነው ያስከተለው። ሞራልና ስነ-ምግባር በጎደለበት አገር ደግሞ ጠንካራና ተከታታይነት ያለው ማህበረሰብ መገንባት አይቻልም። ያም ሆነ ይህ በአሜሪካንና በተቀረው የካፒታሊስቱ ዓለምና በኢትዮጵያ መሀከል የነበረው ግኑኝነት የጌታና የሎሌ ግኑኝነት ሲሆን፣ እንደ ወያኔ የመሰለውን የሞራልና የምሁራዊ ብቃትነት የጎደለውን ኃይል በመጠቀም ጠቅላላውን ህብረተሰብ ማናጋትና እርግጠኝነት እንዳይኖረው ማድረግ ዐይነተኛው የኢምፔሪያሊስቶች ስትራቴጂ ነው። ስለሆነም አሜሪካንም ሆነ የተቀረው የካፒታሊስቱ ዓለም ኢትዮጵያን የሚፈልገው ጥገኛው ለማድረግና የሚጭረውን ጦርነት እንድታፋፍምለት ብቻ ነው። የዋሁ ወታደራችንንም በየቦታው በመሄድ ህይወቱን እንዲሰዋ ይደረጋል።

በተለይም ወያኔ ራሱ በጫረው እሳት ለመጨረሻ ጊዜ እንዲደመሰስ ከተደረገ በኋላ የኢምፔሪያሊስቱ ጎራ መጮህ የጀመረው ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ሊያሳምነን እንደሞከረው የዶ/ር አቢያ አገዛዝ ያልተረጋጋ በመሆኑ ሳይሆን የሚጫወትበትና እንደማስፈራሪያ የሚጠቀምበትን ኃይሉ ስለተመታበት ነው። በተጨማሪም ወያኔ 27 ዓመታት ያህል ይሰጠው የነበረውን ክብርና ያዘጋጀለትን የብዝበዛ ስርዓት አዲሱ የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ሊሰጠኝ አይችልም ብሎ በማሰቡም ነው። ከዚህም በላይ አዲሱ አገዛዝ ወደ ቻይና ፊቱን በማዞር ያገለኛል ወይንም እንደልቤ የምፈነጭበትን መድረክ ያሳጣኛል በማለት ብቻ ነው። ይሁንና ግን ይለናል ፕሮፌሰር ብሩክ አሁን አሁን ግፊታቸውን እየቀነሱ መጥተዋል። ግፊቱን ወይም ጭነቱን ማብዛት ምናልባትም የባሰውን የዶ/ር አቢይን አገዛዝ ወደ ቻይናዎች እንዲጠጋ ስለሚያደርገው በዚህ ዐይነቱ ሁኔታ አይቀጥሉም ይለናል። በሌላ ወገን ደግሞ ቻይናዎች በኢትዮጵያም ሆነ በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ስር የሰደደ የኢኮኖሚ ግኑኝነት በመፍጠራቸው እነሱን መቋቋም እንደማይቻል ፕሮፌሰር ብሩክ ያምናል። የኢኮኖሚ ፕሮጀክትን ሁኔታ ሲያነሳ ቻይናዎች በአገራችንም ሆነ በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ፕሮጀክቶች ከአሜሪካኖች ጋር ሲወዳደር ርካሽ ነው ይለናል። ይሁንና ግን ይህንን ለማወዳደር አሜሪካኖች በኢትዮጵያም ሆነ በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በምን በምን ዐይነት ፕሮጀክቶች እንደተሳተፉ ግልጽ ያደረገው ነገር የለም። ሀቁ ግን በ70 ዓመታት የኢኮኖሚ ዕርዳታ ታሪክ ውስጥ አሜሪካንም ሆነ የተቀሩት የካፒታሊስት አገሮች በትላልቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ በተለይም እንደ ባቡር ሃዲድ ግንባታ በመሳሰሉት ውስጥ ተሳትፈው አያውቁም፤ ፍላጎታቸው አልነበረም። ለምሳሌ ፕሬዚደንት ኔሬሬ ስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ታንዛኒያን ከሞዛምቢክ ጋር የሚያገናኘውን የባቡር ሃዲድ ለመስራት በመጀመሪያ የጠየቋቸው ምዕራቦችን ነበር። እነሱ ግን አሻፈረኝ በማለታቸው ቻይናዎች እንደሰሩ ይታወቃል። ቻይና በኢኮኖሚ የኃያልነት ሚናን መጫወት ከጀመረችበት ከ20 ዓመታት ወዲህ ደግሞ ሆን ብላ የምትሰራው የባቡር ሃዲዶችን ነው። ከዚህ ሃቅ ስንነሳ የምዕራቡ ዓለም የሚሰጠውን ዕርዳታና ቻይና በቀጥታ መዋዕለ-ነዋይ በመሳተፍ የምትጫወተውን ሚና ማወዳደር አይቻልም።

ለማንኛውም አሜሪካም ሆነ የተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም የከፈተው የስነ-ልቦና ጦርነት ወያኔን በመደገፍና በማስታጠቅ የፈጸመውን ወንጀል ለመሸፈን ሲል ብቻ ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያ ካለ ምዕራቡ ዕርዳታ ለመኖር እንደማትችል ማሳመንና መንፈሰ ደካማ ማድረግ ዋናው የስነ-ልቦናው ጦርነት ስትራቴጂ አካል ነው። በዚህም መልክ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን በሁሉም አቅጣጫ በመወጠር ወደ እርስ በርስ ጦርነት የሚያመሩበትን ሁኔታም መፍጠር ነው። የህዝብ ፍሰት እነሱን የሚያሳሰባቸው ጉዳይ አይደለም። ኢትዮጵያ ፈራረሰች አልፈራረሰች የአሜሪካንም ሆነ የተቀረው የካፒታሊስቱ ዓለም ጉዳይ አይደለም። ጦርነት፣ ጥንታዊ ታሪክ ያላቸውን አገሮችን ማፈራረስና በካፒታሊስቱ ዓለም የሚመራና ጭራ የሚሆን ዓለም መፍጠር ዋናው ስትራቴጂያቸው ነው። ታላቁና በዓለም አቀፍ ደረጃ ይታወቅ የነበረው ግብጻዊው ኢኮኖሚስት ፕሮፌሰር ሳሚር አሚን እንዳለው የካፒታሊስት ዓለም ዋና ስትራቴጂና ዓላማ ሁሉንም አገሮች ወደ ኒዎ-ሊበራል ትልቁ ገበያ(Neo-Liberal Supermarket) መለወጥ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በየአገሮች ውስጥ አምራችና ፈጣሪ የህብረተሰብ ኃይልን በመፍጠር ባህልና ህዝቦችን የሚያስተሳስሩ ልዩ ልዩ እሴቶችን መገንባት አይደለም።

በአጠቃላይ ሲታይ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ለሲሳይ አጌና የሰጠው መልስ ብዙ ግንዛቤዎች የሚጎድሉትና ክሪቲካልም ያልሆነ ነው። አዲሱን የዶ/ር አቢይን አገዛዝ ደግሞ እንደ ሰላም አምጭና በመደመር ፍልስፍና መሰረት ሁሉንም ኃይል ለመሰብሰብና ዕድገትን እንደሚፈልግ ሰው አድርጎ ነው የሚነግረን።  ሀቁ ግን ዶ/ር አቢይ ስልጣን ከተቀዳጁ ጀምሮ ህዝባችን ሰላም አግኝቶ አያውቅም። በተለይም በአማራው ብሄረሰብ ላይ የሚካሄደው ግድያ መረን ለቋል። ባጠቃላይ ሲታይ አማራው እንደ እንግዳ ነገር እንዲታይ፣ እንዲጠላና በራሱ ላይ እንዳይተማመን እየተደረገ ነው። ሲገደልና ሲፈናቀል ዝምብለህ ተገደል፣ ዝምብለህ ተፈናቀል የሚል ባህል እየተስፋፋ ነው። አማራው በማንነቱ እንዲያፍር እየተደረገ በሁሉም አቅጣጫ ዘመቻ እየተካሄደበት ነው። በአማራው ላይ የሚደረገውን ጭፍጨፋና ዘመቻ አስመልክቶ ፕሮፌሰሩ አንዳንድ ቦታዎች ግጭቶች አሉ ከማለቱ በስተቀር የደረሰውን ሰቆቃና መፈናቀል በማዘን ለመናገር ዝግጁ አልነበረም። ይህን ያህልም ቁጥር ውስጥ ሊገባ የማይችል ነገር እንደተደረገ አድርጎ ነው ዳሰስ አድርጎ ያለፈው። ጋዜጠኛውም ይህንን በሚመለከት ረገጥ አድርጎ አልጠየቀውም።

ለማንኛውም ዶ/ር አቢይ ስልጣን ላይ ከወጡ ወዲህ ጥቂት የማይባሉ ቤተክርስቲያናት ተቃጥልዋል፤ ብዙ ምዕመናንም በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። ይህንን ጉዳይ በሚመለከት አንድም ቦታ ላይ ፀፀት አላሳዩም፤ ዘመዶቻቸው የተገደሉባቸውንም አላጽናኑም። አንድ የአገር መሪ መስራትና ማድረግ የሚገባውን ነገር አላዳረጉም። የዲሞክራሲንና የነፃነትን ጉዳይ ስንመለከት ደግሞ ዶ/ር አቢይ ሁሉን አውቃለሁ በማለት ወደ አምባገነነት የመጡበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በተለይም ለኦሮሞ ጽንፈኞች ቦታውን በማመቻቸትና እንደልባቸው እንዲፈነጩ በማድረግ በህዝባችን ዘንድ መረጋጋት እንዳይፈጠር ለማድረግ በቅተዋል። ሰላምና መረጋጋት ከሌለ ደግሞ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሊኖር አይችልም። ኢኮኖሚው በሁሉም አቅጣጫ የመዳበርና የመስፋፋት ዕድል ካላገኘ ደግሞ የስራ መስክ መክፈትና ማህበራዊ ጥያቄዎችን መፍታት በፍጹም አይቻልም። በአጠቃላይ ሁኔታውን ስንመለከት አንድ የተገለጸለትና ዲሞክራሲያዊ መንግስት መስራት ያለበትን ነገር አይደለም የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ተግባራዊ የሚያደርገው። አገራችን በጠንካራ መሰረት ላይ እንዳትገነባ የሚወስደው ሳይንሳዊ መሰረትና ጥበብ የጎደለው ፖለቲካ ከፍተኛ አለመረጋጋትን ፈጥሯል። በህዝቡ ዘንድ መረበሽ ይታያል። ዶ/ር አቢይ በሚከተሉት የከፋፍለህ ግዛውና ወዳጅን ከጠላት በደንብ የማይለይ ፖለቲካቸው አገራችንንና ህዝባችን በአስተማማኝ ሁኔታ ውስጥ እንዳይኖሩ ለማድረግ በቅቷል። በዚህ ዐይነቱ ፖለቲካቸውም ምን ዐይነት አገር ለመገንባትና ጥለው ለመሄድ እንደሚፈልጉ ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ ፖለካቸውና የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸው አገራችንን ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚያዳክም ነው። በተለይም ሱዳን እንድትወረን የተደረገውና፣ አረቦች በመዋዕለ-ነዋይ ስም እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ይህ ሁሉ ኢትዮጵያን እንደ አገርና እንደ ማህበረሰብ እንድትገነባ የሚያደርጋት አይደለም። ስለሆነም የፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ትንተና የተሳሳተና የሚያሳስትም ነው። የአገራችንን የውስጡንም ሆነ የውጭውን ፖለቲካ፣ በተለይም ደግሞ የምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም የሚከተለውን የተወሳሰበና አግሬሲቭ ፖለቲካ ግንዛቤ የሚያስጨብጠን ትንተና አይደለም። መልካም ግንዛቤ!

                                                                   fekadubekele@gmx.de

Links

FORUM – Inforadio
Drama oder Chance –
Folgen des Ukraine-Kriegs für Afrika


(Bild: rbb/Matthias Schirmer)

Beitrag: Audiodatei

Weitere Links:

Books

African Predicaments & the Method of solving them effectively

 

(English) Book – 30. August 2016


 

Deutsch – Amharisch / Amharisch – Deutsch

von Fekadu Bekele und Bosena Negussie | 25. Januar 2019

 

 

Capitalism

Fekadu Bekele

 


Fekadu Bekele

Gesellschaftsformation und Artikulation von Produktionsweisen in Äthiopien